ሞዴል ብሎኮችን መፍጠር ፅዱ፣ ምቹና ውብ የመኖሪያ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ የአኗኗር ዘይቤን በማዘመን ጤናዉ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር የላቀ አስተዋፅዖ ያለው መሆኑ ተገለጸ።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አስተዳደር የተቀናጀ ሞዴል ብሎክ ምርቃትና ከነዋሪዎች ጋር የርክክብ መርሃ ግብር ተካሄደ።
በመርሃ ግብሩ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይከበር ስማቸው እንደተናገሩት ከተማችን አዲስ አበባ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል በመሆኑም ህብረተሰቡ አካባቢውን በማስዋብ ለኑሮ ምቹ ውብና ተስማሚ በማድረግ ሞዴል አካባቢን በመፍጠር በመስራት አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነ ሲሆን ለዚህ ማሳያ በዛሬው ዕለት የተመረቀው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አስተዳደር የተቀናጀ ሞዴል ብሎክ ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።
የሞዴል ብሎክን መፍጠር ብቻ ሳይሆን ማጠናከርና ማዝለቅ የሚቻለው ሞዴል ቤተሰብ በየብሎኩ መፍጠር ሲቻልና የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን መንከባከብ ብሎም ለፅዳትና ውበት ስራዎች በሀብትና በጉልበት አስተዋፅዖ የሚያበረከቱ ነዋሪዎች ሲበዙ በመሆኑ ሁሉም ነዋሪ የበኩሉን ማበርከት ይገባል ብለዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ጎዴቦ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው የነዋሪውን ሁለንተናዊ ልማትና ብልጽግና የሚያረጋግጡ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል ከነዚህም አንዱ ሞዴል አካባቢ ፣ ሞዴል መንደርና ሞዴል ቤተሰብ በመፍጠር ነዋሪዎች ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብታቸው በመሆኑ ሁሉም ለልማቱ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በቀጣይም ማህረሰቡ የሚኖርበትን ብሎክ የተሟላ፣ ለህፃናት ምቹና ዘመናዊ መጫወቻ ያለዉ እንዲሆን በማልማት፣ በማፅዳት፣ በማስዋብ፣ ሠላማዊ ከባቢ በመፍጠር፣ ክ/ከተማዋ ብሎም መዲናችን አዲስ አበባ ለመኖርያ ምቹና ተመራጭ እንድትሆን ቀጣይንነት ባለዉ መልኩ ማልማት ያስፈልጋል ብለዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አንዱዓለም አሸብር በበኩላቸው በወረዳው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን የተቀናጀ ሞዴል መንደር መፍጠር አካባቢውን ውብ ጽዱና ማራኪ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች ፣ የጸጥታ አካላት ፣ የሰላም ሰራዊት አባላት ፣የአካባቢው ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።